የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በይፋ ስራውን ጀመረ፤

የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በይፋ ስራውን ጀመረ፤

 የተገኙ ድሎችን በእውቀት መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ፡፡

ክቡር የኢ.... ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲን በመረቁበት ወቅት እንዳስገነዘቡት በአገሪቱ የተገኘውን ድል በዕውቀት መደገፍ የሁሉም የቤት ስራ ሊሆን ይገባል ያሉ ሲሆነ በተገኘው ድል አሁን ባለንበት መንገድ ከቀጠልን ያለምንም ጥርጥር ክልሉንም ሆነ ሀገሪቱን መለወጥ እንደሚቻል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ዩኒቨርስቲውን የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንደሚያደርሱት እምነታቸው መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርስቲው አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በዕለቱ የተመረቀው የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ በርካታ ምሁራንን ባፈራው የቄለም ወለጋ አካባቢ አሁን አሁን እየተዳከመ የመጣውን የምሁራን ምንጭነት ለማስቀጠል ምቹ እድል በመሆኑ አዲሱ ትውልድ ይህን ታሪክ ማደስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ክቡር የኢ.... ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ትምህርትን በተለያዩ አካባቢዎች ፍትሀዊ በሆነ መልኩ በማስፋፋት በተከናወነው ተግባር በቀጥታ በትምህርት ሚኒስቴር የሚተዳደሩ 45 ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 50 ዩኒቨርስቲዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎቹም 30 ሺህ መምሀራንና ተመራማሪዎች ይዘው 800 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በመደበኛነት በመጀመሪያ ዲግሪ ፣በሁለተኛ ዲግሪና በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር በማስተማር ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በዕለቱ ለምርቃት የበቃው የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 2012 መጨረሻ ምሩቃንን ለማፍራት ሥራ ከጀመሩ 11 ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደለሳ ቡልቻ በበኩላቸው በይፋ የተመረቀው የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ለዘመናት የቆየ የአካባቢውን ህዝብ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ጠቁመው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት፣የምርምርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል በመገንባት 2019 ከአገሪቱ ተመራጭ 10 ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘገባ ያመለክታል፡


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡