የወለጋ ዩኒቨርሲቲ፡ የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮችን ከማካተት እና ሴቶችን ከማብቃት ረገድ

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ፡ የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮችን ከማካተት እና ሴቶችን ከማብቃት ረገድ

የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮችን በማካተት እና ሴቶችን በማብቃት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ 2010 የትምህርት ዘመን በዕቅድ አፈጻጸም 2 ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች የአንደኝነት ደረጃ ይዟል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮችን ከማካተት እና ሴቶችን ከማብቃት አንጻር ክፍተቶችን በመሙላት፣ ሴቶችን በማብቃት፣ የአከባቢው ሴት ተማሪዎችን ለመርዳት ያቀደውን ዕቅድ ግብ ለማሳካት በህግና በመመሪያ በማስደገፍ የሴቶችን እኩልነት እና ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መምጣቱን የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር / መርጊቱ ደበላ አብራርተዋል፡፡ ለዚህም ከተማሪ እስከ ከፍተኛ አመራር ያሉት የትምህርት ባለድርሻ አካላት ርብርቦሽ፣ የከፍተኛ አመራሩ ፈጣን ምላሽ እና የወንዶች አጋርነት የስኬቱ ልዩ ምስጥር እንደሆነ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

 በአመራር፣ በአካዳሚ እና በማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ በሰፊው በመስራት ዳይሬክቶሬቱ አመርቂ ውጤት እያመጣ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተማሪዎች እና አመራሮች ተብራርቷል፡፡ የተሠሩ ስራዎች ጉብኝት ወቅት የስርዓተ-ጾታ ዳይሬክቶሬት ባልደረቦች፤ የሴት ተማሪዎች ተወካይ ተማሪ ጫልቱ፣ / አያንቱ መኮንን፣ / ረድኤት ስጦታው፣ መምህርት ሰርካለም ሞላ፣ መምህርት ማህሌት ጋሻው ዳይሬክቶሬቱ ሴት ተማሪዎችን ጨምሮ ለመምህራን፣ ለአመራር እና ማህበረሰቡ ውስጥ ለሚገኙ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ እና በዚህም ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

 ከታሪክና ልምድ የወረስነው አሁንም ላለመላቀቅ እየተፈታተነን ያለውን የስርዓተ-ጾታ ጉዳዮችን አስመልቶ የተዛባ አመለካከት ለመምከን ሳይከፈላቸው መደበኛ ስራቸው ላይ ደርበው በራሳቸው ነጻ ፈቃድ በዳይሬክቶሬቱ እያገለገሉ ያሉ ሠራተኞች ጎለተው ይታዩ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች እና የሴት ተማሪዎች የስነ-ልቦና ችግሮች ላይ በመስራት እንዲሁም አገልግሎቶችን በማሟላት ስኬት አስመዝግበው የዩኒቨርሲቲውንም ስም ላስጠራው የስርዓተ-ጾታ ዳይሬክቶሬት አድናቆት እና ምስጋና የቸሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤባ ሚጀና ናቸው፡፡ዶክተሩ የዩኒቨርሲቲውን ጥሩ ተምክሮ ለመጎብኘት በቦታው የተገኘውን የትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ-ጾታ ዳይሬክቶሬት እና ባልደረቦችን ጨምረው በማመስገን ድጋፍና ክትትሉ ቀጣይነት እንዲኖረው አክለውበታል፡፡

 በሰነድ ከተቀመረው በላይ መሬት ላይ ያሉ በተግባር የሚታዩ ስራዎች የበለጠ እራሳቸውን የሚገልጹ መሆኑ ዳይሬክቶሬቱ ከዳይሬክተሯ ጨምሮ በመተሳሰብ እና በመተጋገዝ ለዚህ ውጤት እንደደረሰ የገለጹት በኢ.... ትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ-ጾታ ዳይሬክቶሬት ባልደረባ አቶ እስክንዲር ላቀው ናቸው፡፡ አቶ እስክንዲር አክለውም ለዳይሬክቶሬቱ ስኬታማነት የተባበሩትን አካላት በማመስገን በቀጣይነት የበለጠ ስኬት በማስመዝገብ አርዓያነታቸውን እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

 2025. 25 ምርጥ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ እሰለፋለሁ ብሎ ባስቀመጠው ራዕይ መሠረት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በስርዓተ-ጾታ ጉዳዮች ላይ ብዙ ስራ የሠራ ሲሆን ከእነዚህም ለአርዓያነት ለሰራተኞች ደረጃውን የጠበቀ የህጻናት ማቆያ፣ ለሴት ተማሪዎች የመወያያ ክፍል እና በሴቶች ማደሪያ አካባቢ በየህንጻዎች ስር የማንበቢያ ክፍሎች፣ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ የጠረጴዛ ቴኒስና ሌሎች ፋሲሊቲዎች መሟላታቸው ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ሞዴል እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡