የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ለሴቶች ይከብዳል ብሎ መወሰን ስህተት እንደሆነ ተጠቆመ

የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ለሴቶች ይከብዳል ብሎ መወሰን ስህተት እንደሆነ ተጠቆመ

የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች መሠረታዊ የሂሳብ ስሌትን በተደጋጋሚ መስራት የሚጠይቅ እንጂ ለሴቶች ይከብዳል ብሎ መወሰን ስህተት እንደሆነ ተጠቆመ፡፡
በኢንጂነሪንግ ትምህርት ውጤታማ ለመሆን የተማሪዎች የህሳብና የፊዚክስ ዕውቀት መሠረት መሆኑንም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሲቪል ኢንጂነሪንግ መምህርት አስኳል ግርማ ይገልጻሉ፡፡
እንደ መምህርቷ ገለጻ የኢንጂነሪንግ ትምህርት የህሳብ መሠረታዊ ስሌቶችን በተደጋጋሚ መስራት የሚጠይቅ እንጂ ከሌላው ትምህርት በተለየ ሁኔታ የሚከብድ ሆኖ ለሴቶች አይመችም በማለት መፈረጅ እንደሌለበት እና ስህተት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ለትምህርቱ መሠረት የሆኑትን የሂሳብና ፊዚክስ ትምህርቶች ላይ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ተማሪዎችን ኮትኩቶ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ቅድስት ታምራት 3 ዓመት የሂሳብ ትምህርት ተማሪ እና ነፊዛ ሸምሱ 3 ዓመት የፊዚክስ ትምህርት ተማሪ ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለሴት ተማሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እገዛ በማድረጉ ወደ ዩኒቨርሲቲ ይዘው የመጡትን ከፍተኛ ነጥብ ይዘው እንዲቀጥሉ እንዳስቻላቸው በማብራራት የመምህርቷን ሀሳብ ይጋራሉ፣ በሳይንስ ትምህርት ይበልጥ ለፊዚክስና ለሂሳብ ትምህርቶች ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ተማሪዎችን ኮትኩቶ ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ-ጾታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር / መንበረ /ጻዲቅ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሁሉ ማበረታቻ፣ ፋሲሊቲዎችን እና የተለያዩ ፈተናዎች ማቋቋሚያ ካውንሲሊንግ ስራ በማሟላት እገዛ በማድረግ ሴት ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡