በአነስተኛ ግብዓት ከፍተኛ ውጤት በሃይሌ ቡባሞ ትምህርት ቤት

በአነስተኛ ግብዓት ከፍተኛ ውጤት በሃይሌ ቡባሞ ትምህርት ቤት

በብዙሃኑ ዘንድ በድሮው አጠራሩ ሆሳዕና ቁጥር አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመባል ይታወቃል የአሁኑ ሃይሌ ቡባሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፡፡ ትምህርት ቤቱ የሚገኘው በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ክልል በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ ሲሆን የተመሠረተው 1945. ነው፡፡ ሃይሌ ቡባሞ የሀዲያ ዞን ተወላጅና ለዞኑ ትምህርት ብልጽግና ብዙ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ለዚህ ድርጊታቸው ማስታወሻነት ትምህርት ቤቱ 1994. በስማቸው እንዲጠራ ተሰየመ፡፡
የሃይሌ ቡባሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 2009. በትምህርት ስራ አፈጻጸም በክልሉ ካሉት ሁሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ እንደ ክልል ቢሎም እንደ ፌዴራል መንግስት ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የትምህርት ቤቱን ውስጠ አሰራር ለማያውቀው ሰው የትምህርት ቤቱ ውጫዊ ሁኔታ ግርምት ሳይፈጥርበት አይቀርም፡፡ ብዙ ህንፃዎችና በቂ የመማር ማስተማር ፋሲሊቲዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ባለው ነገር ብቻ የውስጥ አሰራርና አደረጃጀት በማቀናጀት፣ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በአንድ እስትንፋስ የተማሪ ውጤት ላይ መረባረባቸው ትምህርት ቤቱ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ለሽልማት መብቃቱን የከተማው ትምርት /ቤት ሃላፊ አቶ ኤርዶሎ ዲጋ ይገልጻሉ፡፡
2008. ነባር ችግሮችን ነክሰው በማውጣት ሁሉም እንዲወያይበት መደረጉ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው እንዲሁም በቁጭትና በእሊህ እጅ ለእጅ በመያያዝ ጠንክረን በመስራት ለዚህ እንዲንበቃ ረድቶናል ይላሉ የትምህርት ቤቱ ርዕሠ መምህር አቶ መለሰ አባካ፡፡ ትምህርት ቤቱ የነበሩትን እንቅፋቶች በጋራ ስምምነት በማስወገድ ለደረጃ እንደበቃ የሀዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሀብቴ ሀሳቡን ይጋራሉ፡፡
በሁሉም የህዝብ ክንፍና በመንግስት ክንፍ ጠንካራ የልማት ቡድን አደረጃጀት ላይ የተመሠረተ ትምህርት ቤቱ፣ የልማት ቡድኖችና አደረጃጀቶቹ በሚያቀርቡት እቅድ መሠረት ክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ ይደረግላቸዋል፣ የልማት ቡድኖቹ እና አደረጃጀቶቹ እርስ በርስ መተራረማቸው ከትምህርት ተሳትፎ እስከ ትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ማረጋገጥ ረድቶናል የሚሉት የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሠ መምህራን አቶ ፀደቀ አበቴ እና አቶ ደስታ ገዴ ናቸው፡፡
የትምህርት ቤቱ .... ሰብሳቢ አቶ አመርጋ ዳራጎ የትምህርት ቤቱን የስነ ምግባር ብስለት ሲያጋሩ ተማሪዎችና መምህራን ጨምሮ በትምህርት ቤቱ ባህል የተሳሳተ ወይም ያጠፋ አካል ቢኖር ወዲያው ይቅርታ በመጠያየቅ ወደ ነባር ሁኔታ ይመለሳል ይላሉ፡፡ በትምህርት ሰዓት ከተማሪ ስነ-ምግባር የተነሳ በግቢው ውስጥ ጸጥታ የበዛ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤቱ ብዙ ችግሮች እንዲፈቱለት ይሻል፡፡ ከእነዚህም የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ፣ የውሃ አቅርቦት ችግር፣ የመማሪያ ክፍሎች ጥበትና ወደ ህንጻ መቀየር፣ የበጀት/ፋይናንስ እጥረት ... ሲሆን ትምህርት ቤቱ ደረጃውን አስጠብቆ እነዚህን ችግሮች በማስወገድ ወደ ፊት ይራመድ ዘንድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በየደረጃው ያሉት አካላት ትኩረት በመስጠት ችግሮቹን እንድጋሩ ትምህርት ቤቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
እኛም ሃይሌ ቡባሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁኔታዎች መደላድል ሳይጠብቅ አኩሪ ታሪክ እንደስመዘገበ ሁሉ አሁንም ታሪኩን መድገም አለበት እንላለን፡፡


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡