የመምህራን ትምህርት ስልጠና የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የልህቀት ማዕከላት ተመረጡ

የመምህራን ትምህርት ስልጠና የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የልህቀት ማዕከላት ተመረጡ

የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ የመምህራንና የትምህርት አመራር ስልጠና ስርዓት ከዚህ በፊት ከነበረው ይበልጥ በተሻለ መልኩ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሦስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የልህቀት ማዕከላት ሆነው መመረጣቸውን የኢ... ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ የኢ... ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር / ጥላዬ ጌቴ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ አምስተኛውን የትምህርት ልማት መርሃ ግብር ለማሳካት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የመምህራን አሰለጣጠን ስርዓትና አደረጃጀትን ማሻሻል ወሳኝ መሆኑን በማመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለልህቀት ማዕከልነት ለመምረጥ ለውድድር በወጣው የፍላጎት መጠየቂያ መሰረት፣ ከሰባት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች የምዘና መስፈርቱን በማሟላት መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደሚኒስትሩ ገለፃ የመምህራንና የትምህርት አመራር ስልጠና የልህቀት ማዕከላት በመሆን ተወዳድረው የተመረጡት ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና መቐለ ዩኒቨርሲቲ ሲሆኑ ወደ መምህርነት ሙያ ለመሰልጠን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ፍላጎትን ያገናዘበ መሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
/ ጥላዬ አክለውም በመምህርነት ሙያ ለማሰልጠን የተመረጡት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፥ እጩ መምህራንን በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት ይዘትና የማስተማር ዘዴ ከማሰልጠን ጎን ለጎን የመምህራንና ትምህርት አመራር ስልጠና ስትራቴጂ የአሰለጣጠን ስርዓትን የማጥናት፣ የሙያ ደረጃዎች የማውጣትና የማሻሻል፣ የስርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ዝግጅት ስራዎች እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡
ተማሪዎች የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችሎታ ማዳበር እንዲችሉ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሁሉንም የትምህርት አይነቶች የሚያስተምሩ መምህራን በበቂ የማስተማሪያ ዘዴዎች በማሰልጠን፣ ለተማሪዎች እውቀት እንዲያስተላልፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንን ከማሰልጠን ረገድ ሀገራዊ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ከተመረጡ ተቋማት የተውጣጡ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩም በኢ... ትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ እና የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም ከተመረጡት የልህቀት ማዕከላት ጋር የስምምነት ሰነድ ፊርማ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት መግለጫውን ተከታትሎ በዘገበው መሰረት፣ የተመረጡ የልህቀት ማዕከላት በተያዘው 2010 ትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው የማሰልጠን ስራ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡