ለአይነስውራን መምህራን የኮምፒውተር አጠቃቀምና ለትምህርት አመራሮች የምልክት ቋንቋ ስልጠና ተሰጠ።

ለአይነስውራን መምህራን የኮምፒውተር አጠቃቀምና ለትምህርት አመራሮች የምልክት ቋንቋ ስልጠና ተሰጠ።


በስልጠናው የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር / አሰፋሽ ተካልኝ "የትምህርት ፍትሀዊነትንና ተደራሽነትን ከማስፋፋት አንጻር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው መምህራንና ተማሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።ለዚህም አንዱ ማሳያ ዛሬ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁት አይነስውራን መምህራን ዘመኑ ከሚፈልገው ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተዋወቅ እንዲቻል ጃውስ(Jaws)በሚባል ሶፍትዌር በመታገዝ በድምጽ ኮምፒውተርን መጠቀም የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል"
ስልጠናው ባለፉት ሁለት ተከታታይ ክረምት በተመሳሳይ መልኩ የተሰጠ መሆኑን አስታውሰው የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት በመስራት አሁን ካለው ቁጥር በላይ ለማሰልጠን እቅድ መያዙንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ወልደማርያም በበኩላቸው ይህንን ስልጠና ያጠናቀቁ መምህራን ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ስራ ቦታቸው ሲመለሱ ወደ ተግባር በማውረድ ተማሪዎችን የሚረዱበት ዜጎችንም የሚያገለግሉበት እንዲሆንና ለዚህም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን የሶፍትዌር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸወ ተናግረዋል።
በተለይም የምልክት ቋንቋ የሰለጠኑ መምህራን ያገኙትን እውቀት ለሌሎች መምህራን በማሰልጠን የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲያገለግሉ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።
በስልጠናው ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ 125 አይነስውራን መምህራን የኮምፒውተር አጠቃቀም እና 81 መምህራንና የትምህርት አመራሮች በምልክት ቋንቋ ሰልጥነዋል።

ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡