ዜናዎች ዜናዎች

በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር ባለፉት አራት ዓመታት በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ውጤት ላይ ውይይት ተደረገ

በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቱ ሦስት ክልሎች በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ አተኩሮ ሲካሄድ የቆየው ፕሮጀክት ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ገለጸ፡፡

የፊላንድ መንግስት በትምህርቱ ዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቱ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት በፊንላንድ መንግስት ድጋፍ ሲካሄድ የቆየው ፕሮጀክት አፈጻጸም ግምገማና ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አማካሪ አቶ ብርሀኑ ሞረዳ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የመምህራን ትምህርትን በመደገፍ፣የአካቶ ትምህርት ድጋፍ ሰጪ ማዕከላትን በማጠናከርና አገር አቀፍ የአካቶ ትምህርት ማስተባበር ዕቅድ ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር . . . 2013 – 2017 በአዲስ አበባ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ በፕሮጀክቱ በተከናወነው ተግባር አበረታች ውጤቶች መገኘቱን አቶ ብርሀኑ ገልጸዋል፡፡

የመምህራን ትምህርት ኮሌጆችና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን አቅም መገንቢያ ፕሮጀክት ላለፉት አራት ዓመታት 16 ማዕከላት በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በአዲስ መልክ ከተከለሰው 2012 የልዩ ፍላጎት ትምህርት ስትራቴጂ ጋር ተቀናጅቶ እንዲተገበር በመደረጉ የመማር ማስተማሩ ሂደት በአካታች ሁኔታ እንዲከናወን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ አግባብነት ያላቸው ባለሙያዎች በሦስቱም ክልሎች የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን ጠቁመው ስራው ወደ ሌሎችም ክልሎች መስፋት እንደሚችል በመረጋገጡ በቀጣይም ወደ ሌሎች ክልሎች በማስፋት ፕሮግራሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑንምአብራርተዋል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የፊላንድ ኤምባሲ የኢኮኖሚክና ንግድ ጉዳዮች ትብብር ኃላፊ ሚስተር አርቶ ቫልጃስ በበኩላቸው በሁለቱ መንግስታት ትብብር ላለፉት አራት ዓመታት በሦስቱ ክልሎች ሲተገበር በቆየው በዚሁ ፕሮጀክት በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ጠቃሚ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅም የፊንላንድ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ከመጪው ዓመት ጀምሮም በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በተለይም ለአካቶ ትምህርትና ለልዩ ፍላጎት ትምህርት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚስተር አርቶ ቫልጃስ በዚሁ ጊዜ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ በመንግስት በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በመንደፍ የአካቶ ትምህርትና የልዩ ፍላጎት ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ በቀጣይም በሚያደርገው ጥረት የአገራቸው መንግስት ድጋፍ እንደማይለየው የኤምባሲው የኢኮኖሚክና የንግድ ጉዳዮች ትብብር ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆችና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን አቅም መገንቢያ ፕሮጀክት አማካኝት ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች በዶክመንተሪና በሪፖርት ቀርበው ውይይትና ግምገማ የተደረገባቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡No comments yet. Be the first.
ዜናዎች

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚካሄዱ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች ውጤታማነት ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ወላጆችና ህብረተሰቡ ኃላፊነታቸውን በላቀ ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚካሄዱ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች ውጤታማነት ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ወላጆችና ህብረተሰቡ ኃላፊነታቸውን በላቀ ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ አስታወቁ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረ-ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነት የሚገነባባቸው ተቋማት እንጂ ተግባራቸው በጥቂት ችግር ፈጣሪዎች የሚስተጓጎል አለመሆኑንም ገለጹ 141ሺህ አዲስ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በመማር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከ2011 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም የቅድመ ምረቃ ትምህርት መስኮች የብቃት መለኪያ አጠቃላይ ምዘና (የመውጫ ፈተና) ልተገበር ነው

ከ2011 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም የቅድመ ምርቃ ትምህርት መስኮች ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የብቃት መለኪያ አጠቃላይ ምዘና (የመውጫ ፈተና) ወስደው አጥጋቢና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን በተለይም የምሩቃንን ብቃትና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አጠቃላይ ምዘና ወይም የመውጫ ፈተና መስጠት የምሩቃንን ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለመመዘን የላቀ ሚና ከመጫወቱም በተጨማሪ የተመራቂ ተማሪዎች በራስ መተማመን ያጎለብታል፡፡

የምርምርና የፈጠራ ስራ ውድድር ኤግዚቪሽን ተካሄደ

የሂሳብና ሣይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማዕከል ከስቴምስ ሲነርጂ ፣ከዩኔስኮ እና ከኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር "በሣይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የበለፀገ ህብረተሰብ ለዘላቂ ሠላምና ልማት "በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የምርምርና ፈጠራ ስራ ውድድር ኤግዚቪሽን በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ተካሄደ፡፡ የምርምርና የፈጠራ ስራ አውደ- ርዕይ መከፈቱን አስመልክቶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ የኢትዮጵያን ሣይንስ ለማበልፀግ የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው ይህ ማዕከል የህብረተሰቡን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅሙን ለማጎልበት ለማስተማርና የሣይንስ ፖርሽን ለመፍጠር የተሰራ ሲሆን ቋሚ የሳይንስ ማዕከል ለመፍጠር ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ በመሆኑም በቅርቡም የሳይንስ ማዕከሉ ወደ ስራ ይገባል በዚህም ወጣቱ ወደ ሣይንስ በሄደ ቁጥር የሀገራችን ተስፋ እየለመለመ ይሄዳል ብለዋል፡፡

የሥርዓተ-ፆታ ማካተትና ተቋማዊ ማድረግ መከታተያ፣ መመዘኛና በደረጃ የመለያ ማዕቀፍ ላይ ስልጠና ተሰጠ

የትምህርት ሚኒስቴር ሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሁሉም የሥራ ክፍሎች እና ከተጠሪ ተቋማት ለተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ባለው ስልጠና የሁለተኛ ቀን ውሎ በሥርዓተ-ፆታ ማካተትና ተቋማዊ ማድረግ መከታተያ፣ መመዘኛና በደረጃ የመለያ ማዕቀፍ ላይ ስልጠና ሰጠ ፡፡ ስልጠናውን የሰጡት በዳይሬክቶሬቱ የስርዓተ ፆታ ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አረጋ ሲሆኑ የዚህ ስልጠና ዋና አላማ በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ያሉ የስራ ክፍሎች የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ተቋማዊ ለማድረግ የሚያከናውኑትን ተግባራት በመመዘንና ተከታታይ ድጋፍ በመስጠት የሥርዓተ ፆታ እኩልነት በሁሉም ዘርፍ ለማረጋገጥ ብሎም የሀገራችንን የልማት ራዕይ ለማሳካት ነው ብለዋል፡፡

የመንግስታዊና ግብረሰናይ ድርጅቶች የጋራ ፎረም ውይይት ተካሄደ፡፡

ዛሬ ጥቅምት 20/2010 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር አዳራሽ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትምህርት ስልጠና ዘርፍ የ2010 ዓ.ም ዋና ዋና ዕቅዶች ላይ ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ተገኝተው የመድረኩን አላማ የገለጹት በትምህርት ሚኒስቴር የእቅድ ዝግጅትና ሃብት ማፈላለግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ግርማ የመድረኩ ዋና አላማ የትምህርት ሴክተሩ እቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡