በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር ባለፉት አራት ዓመታት በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ ያስገኘው ውጤት

በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር ባለፉት አራት ዓመታት በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ ያስገኘው ውጤት

በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቱ ሦስት ክልሎች በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ አተኩሮ ሲካሄድ የቆየው ፕሮጀክት ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ገለጸ፡፡
የፊላንድ መንግስት በትምህርቱ ዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቱ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት በፊንላንድ መንግስት ድጋፍ ሲካሄድ የቆየው ፕሮጀክት አፈጻጸም ግምገማና ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አማካሪ አቶ ብርሀኑ ሞረዳ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የመምህራን ትምህርትን በመደገፍ፣የአካቶ ትምህርት ድጋፍ ሰጪ ማዕከላትን በማጠናከርና አገር አቀፍ የአካቶ ትምህርት ማስተባበር ዕቅድ ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በፊንላንድና በኢትዮጵያ መንግስታት ትብብር . . . 2013 – 2017 በአዲስ አበባ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ በፕሮጀክቱ በተከናወነው ተግባር አበረታች ውጤቶች መገኘቱን አቶ ብርሀኑ ገልጸዋል፡፡
የመምህራን ትምህርት ኮሌጆችና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን አቅም መገንቢያ ፕሮጀክት ላለፉት አራት ዓመታት 16 ማዕከላት በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በአዲስ መልክ ከተከለሰው 2012 የልዩ ፍላጎት ትምህርት ስትራቴጂ ጋር ተቀናጅቶ እንዲተገበር በመደረጉ የመማር ማስተማሩ ሂደት በአካታች ሁኔታ እንዲከናወን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ አግባብነት ያላቸው ባለሙያዎች በሦስቱም ክልሎች የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን ጠቁመው ስራው ወደ ሌሎችም ክልሎች መስፋት እንደሚችል በመረጋገጡ በቀጣይም ወደ ሌሎች ክልሎች በማስፋት ፕሮግራሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑንምአብራርተዋል፡፡
በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የፊላንድ ኤምባሲ የኢኮኖሚክና ንግድ ጉዳዮች ትብብር ኃላፊ ሚስተር አርቶ ቫልጃስ በበኩላቸው በሁለቱ መንግስታት ትብብር ላለፉት አራት ዓመታት በሦስቱ ክልሎች ሲተገበር በቆየው በዚሁ ፕሮጀክት በአካቶ ትምህርትና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ጠቃሚ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅም የፊንላንድ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ከመጪው ዓመት ጀምሮም በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በተለይም ለአካቶ ትምህርትና ለልዩ ፍላጎት ትምህርት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚስተር አርቶ ቫልጃስ በዚሁ ጊዜ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ በመንግስት በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በመንደፍ የአካቶ ትምህርትና የልዩ ፍላጎት ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ በቀጣይም በሚያደርገው ጥረት የአገራቸው መንግስት ድጋፍ እንደማይለየው የኤምባሲው የኢኮኖሚክና የንግድ ጉዳዮች ትብብር ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆችና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን አቅም መገንቢያ ፕሮጀክት አማካኝት ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች በዶክመንተሪና በሪፖርት ቀርበው ውይይትና ግምገማ የተደረገባቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡