የኢትዮጵያ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራምን አንዱ የአቅም ግንባታ አካል በማድረግ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሟላት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
መንግስት ለዘርፉ የሚያገለግል ፖሊሲና ጠቋሚ ስትራተጂ ለከፍተኛ ትምህርቱ ዘርፍ በማዘጋጀትና ያልተማከለ አደረጃጀትን በመፍጠር ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ በዚህም መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ስትራተጂ ማዕከልን አቋቁሟል፡፡ ይህ ተቋም በ1995 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 86.1 በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሰረት ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በመምራትና በማስተዳደር፡ የተቋማትን ማስፋፊያና ማሻሻያ ፕሮግራሞች በመምራት፡ በማማከር፡ ስትራተጂዎች በመንደፍ፤ እንዲሁም በተለያዩ ጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፤፤