ትምህርት ሚኒስቴር ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስገንባት የ7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ትምህርት ሚኒስቴር ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስገንባት የ7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው ህዳር 14 ቀን 2007 . በዋግኽምራ  ዞን የሚገኘው  የዋግ ልማት ማህበር "ህብረት  ለዋግ ልማት" በሚል ባዘጋጀው ሃገራዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ  የማህበሩን ጥረት ለመደገፍ በዞኑ አንድ ሙሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ቃል በገቡት መሰረት ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እና የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ ግንባታውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። ገንዘቡ የተገኘው ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድጋፍ ሲሆን 1 እስከ 8 ክፍሎች ያሉት አንድ ሙሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡

ከሃያ ዓመታት ወዲህ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲን መሰረት በማድረግ በዞኑ የተሻለ የትምህርት እንቅስቃሴ መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር ጥላዬ  በዚህም ሁለት መሰረታዊ ለውጦች መታየታቸውን ይናገራሉ። የትምህርት ሽፋን እያደገ መምጣቱ እንዲሁም የዞኑ ማህበረሰብ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መምህራንን በማሰልጠንና ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት ትምህርት ሊሰጥ የሚችልበት የሽግግር ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን ነው፡፡16 - Wag Himra News - Pic1

በዞኑ ያለውን የትምህርት ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ታስቦ ድጋፍ መደረጉንና የዋግኽምራ ዞን ትምህርት መምሪያም ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ እንዲያውለው ያስገነዘቡት ሚኒስትር ዴኤታው በትምህርት ቤት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሚኒስቴር /ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና  ግንባታው ሲጠናቀቅ ትምህርት ቤቱ የልህቀት ማዕከል ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የዋግምኽራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ በተረከቡበት ወቅት በዞኑ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ለዋግ ልማት ማህበር ቃል በገባው መሰረት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የሚበረታታና በትምህርት ቤቶቻችን የገፅታ ግንባታ ላይ አሻራ  ያሳረፈ  ነው ያሉት ኃላፊው ተቋሙ ያደረገውን ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ለማዋልና ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የዋግ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ በየነ በበኩላቸው ማህበሩ በዞኑ በመንግስትና በህብረተሰቡ  በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ያሉ ክፍተቶችን በመለየት በተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ በትምህርትና ጤና ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ተናግረው የኢ... ትምህርት ሚኒስቴር ላበረከተው የገንዘብ ድጋፍ በማህበሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ የሚገነባው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባወጣው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ስታንዳርድ መሰረት በዋግኽምራ  ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በጋዝጊብላ ወረዳ አበቃት ቀበሌ በሚባል አካባቢ መሆኑንና ግንባታው በዚህ ዓመት እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡

 


News

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡