የትምህርት ሚኒስቴር ግንባር ቀደምና ታታሪ የፋይናንስ አስተዳደር ሰራተኞች ተሸለሙ

የትምህርት ሚኒስቴር ግንባር ቀደምና ታታሪ የፋይናንስ አስተዳደር ሰራተኞች ተሸለሙ

30 - 2የፋይናንስ አስተዳደር

በትምህርት ሚኒስቴር የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግንባር ቀደሞችና ታታሪ ሠራተኞች ሽልማትና የምስክር ወረቀት ሰጠ::

የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የዕውቅና እና የምስጋና ስነስርዓት በመልካም አስተዳዳርና ሠራዊት ግንባታ፣ የመስሪያ ቤቱን የረጅም ዓመታት ተሰብሳቢ ሂሳብ በማወራረድ፣ሠራተኞችን በማብቃት እንዲሁም የተሰጣቸው ድጋፍና የሥራ ላይ ስልጠና ተጠቅመው የበቁ 10 ሠራተኖች ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ወይሞ በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ዳይሬክቶሬቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዋናዋና ተግባራትና የፋይናንስ ባለሙያዎችን በማብቃት ረገድ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ለሌሎች የተቋሙ ዳይሬክቶሬቶች በተሞክሮነት ለማስተላለፍ የምስጋናና የዕውቅና ስነ ስርዓት ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ 

በዳይሬክቶሬቱ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ያለምንም ክፍተት ለመፈፀም እንዲቻል ሠራተኞችን በሁሉም የፋይናንስ ዘርፍ የማብቃት ስራ መሰራቱን የገለፁት አቶ አለማየሁ አምስት ሠራተኞችን የባንክ ሂሳብ ማስታረቅ የፋይናንስ ሪፖርት ፣ቫት ዊዝሆልዲንግ ፣የፔሮል ዝግጅትና የመሳሰሉት ስራዎች ለመስራት የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለረጅም ዓመታት ሳይወራረዱ የቆዩ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለመቀነስ የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ አለማየሁ በዚህም 230ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብሳቢ ሂሳብ ማወራረድ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የስኬታችን ምስጢር የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች የለውጥ ስራዎችን በሙሉ ልብ በመተግበር እንደ አንድ ሆነው መስራታቸው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ 2009 በጀት ዓመት የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ተግተን መስራት ይጠበቅብናል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ማዕረግ የሚኒስትር ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሴ በየነ የተዘጋጀውን ሽልማትና የምስክር ወረቀት ለተሸላሚዎቹ ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞችና ባለሙያዎች ደንበኛን ለማርካት ለተቋማችን ዕድገትና ለአገራችን መለወጥ እየሰራቹ መሆኑን የሚያመላክት ውጤት አስመዝግባችኋል እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ያስመዘገበው ውጤት የአስተሳሰብ ለውጥ እየመጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ ንጉሴ እርስ በርስ መማማርና ሌሎችን ማብቃት በስራ አለም ውስጥ ለውጤት የሚያበቃ ተግባር በመሆኑ የክፍሉ ባለሙያዎች ይህንን አኩሪ ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡


News

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡