"አንድም ህፃን ከትምህርት ገበታ ውጪ እይሆንም"

"አንድም ህፃን ከትምህርት ገበታ ውጪ እይሆንም"

 

የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ 2008 . የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈፃፀም የጋራ ግምገማ በጅግጅጋ ከተማ ቀርያን ዶደን መታሰቢያ አዳራሽ በድምቀት ተካሂዷል፡፡ የግምገማ መድረኩ በዋናነት በትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ግንባታ፣የክልላዊና ብሔራዊ ፈተናዎች ቅድመ ዝግጅት፣የመምህራን የደመወዝ እድገትና የመኖሪያ ቤት እንዲሁም የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች፣መጠነ መድገማና ማቋረጥን ለማስቀረት የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም በዓመቱ ሊከናወኑ በታቀዱ ሌሎች ተግባራት ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡

በጋምቤላ ክልል በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን በመጡ ታጣቂዎች ለተገደሉትና በሶማሌ ክልል በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረውን የግምገማ መድረክ በንግግር የከፈቱት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባስተላለፉት መልዕክት መድረኩ የተዘጋጀው በዓመቱ የታቀዱ የትምህርት ግቦች ያሉበትን ሁኔታ ለመፈተሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የትምህርትና የቴክኖሎጂ ሠራዊት በመገንባት የትምህርት ግቦችን በማሳካት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችና የተመዘገቡ ስኬቶች መገምገም የመድረኩ ተልዕኮ መሆኑንም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ መጠነ መድገምና መጠነ ማቋረጥን በህዝብ ክንፍ በመታገዝ ለማስቀረት የያዝናቸውን ግቦች በተመለከተ ያደረግናቸውን እንቅስቃሴዎችና የደረስንበትን ደረጃ እንገመግማለን ብለዋል፡፡

‹‹አንድም ህፃን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆን እናደርጋለን›› በሚል የገባነውን ቃል ከግብ ለማድረስ ያከናወንናቸውን ተግባራት እንዲሁም የትምህርት ጥራት ግብዓቶችን በተደራጀ የሠራዊት እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች በጥልቀት እንደሚፈተሹም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የሚሰጡትን ብሔራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ዝግጅትበተመለከተም የትምህርት ጥራትን የሚገዳደር ፈተና ኩረጃን ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚደረግም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ትምህርት ላቋረጡ ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ድጋሚ 10 እና 12 ክፍል ብሔራዊና ክልላዊ ፈተናዎች የምንሰጥ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለተማሪዎች፣ወላጆችና መምህራን ማሳወቅ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ የመምህራንን የመኖሪያ ቤትና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል የደመወዝና የመኖሪያ ቤትአቅርቦት በተመለከተ ጥናቶች ተጠናቅቀው ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት የተላለፈ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ያለበትን ደረጃ በመድረኩ በመገምገም በሚቀጥሉት ጊዜያት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መታሰቡንም አስታውቀዋል፡፡

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ኡመር በበኩላቸው በህዝቦች መስዋዕትነት የክልሉ ህዝብ መብቱን ቢጎናፀፍም በክልሉ የነበሩ አንዳንድ ፀረ ሰላም ሃይሎች ሲፈጥሩት በነበረው ችግር ምክንያት የልማት ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አውስተው ባሁኑ ወቅት ክልሉና የፌዴራሉ መንግስት በመተባበር ባደረጉት ጥረት በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት ማዞር ችሏል ብለዋል፡፡  የክልሉ መንግስት በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በትምህርት፣በጤና፣በውሀ፣ በመንገድ ግንባታና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ባከናወናቸው ተግባራት የክልሉ ህዝብ የሰላም የልማት ተጠቃሚ መሆን መቻሉንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡ ክልሉ 2008 . የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ መፃህፍት አሳትሞ የማሰራጨት ፣መማሪያ ክፍሎችና ሌሎች ግብዓቶች የማሟላት ስራ መሰራቱንም አቶ አብዲ አስታውቀዋል፡፡

መድረኩ በሁሉም ክልሎችና ሁለት መስተዳድሮች ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን የሚያሳይ ሪፖርት በማዳመጥ ውይይት እንደሚያካሂድ ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡


News

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡