የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

 

የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የጋራ የግምገማ መድረክ በሐረር ከተማ ከጥር 23-25/2008 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የግምገማ መድረኩን አብይ ጉዳዮች ሲያብራሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በሀገራችን ዘላቂ የትምህርት ልማት ግቦች ትኩረት ከተሰጣቸውና ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነት ለማዳረስ ከሚሰሩ ሥራዎች አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልፀው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ስርዓታችን ሃገራችን የምትፈልገውን  ዓይነት ሰው መፍጠር ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ የትምህርት ጥራትን  ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተግተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በቅድሚያ ፊደልና ቁጥር የለዩ እንዲሁም ማንበብና መፃፍ የሚችሉ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ይኖርብናል ያሉት አቶ ሽፈራው ይህ ካልሆነ የትምህርት ጥራት ተግዳሮቶችን መቅረፍ እንደማይቻል ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሥርዓታችን አደጋ ለሆነው ኪራይ ሰብሳቢነት መሸሸጊያ ሆኖ እንዳያገልግል ለማምከን የሚያስችሉ የትምህርት ሴክተር የንቅናቄ ማቀጣጠያ መድረኮች ሲካሄዱ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሩ መድረኮቹ ያስገኙት ውጤት ቢኖርም የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ፡፡

ባለፉት ዓመታት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ ከማሳደግ አንፃር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ የትምህርት ማቋረጥ፣ መድገምና ያለማጠናቀቅ ችግሮች ዋነኞቹ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ተግዳሮቶች መሻሻል ማሳየታቸውንና በቀጣይም የሚቀረፉበትን መንገድ በማመቻቸት ወደ ተጨባጭ ለውጥ ልንሸጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል። የሀረሪ ህዝብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ አብዱልማሊክ በከር መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ ትምህርት ቀጣይነት ላለው እድገት መሰረት መሆኑን ጠቁመው አገራችን የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ የሚቻለው በትምህርት ልማት አማካይነት በትክክለኛ እውቀትና ክህሎት ታንጾ፤ በሳይንሳዊ አስተሳሰብና ዴሞክራሲያዊ ባህል የተገነባ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን መፍጠር ስንችል ነው ብለዋል።

የሀረሪ ክልላዊ መንግስት ባለፉት አመታት ለትምህርት ልማት ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በመመደብና ልዩ ድጋፍ በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን የጠቆሙት አፈጉባኤው በተለይ የትምህርት ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ርብርብ በመደረጉ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የነበሩትን የሁሉንም ፓኬጆች አተገባበርና ሂደት፤ ያሉ ድክመቶችና ጥንካሬዎች ፈትሸንና ለይተን ወደፊት በተደራጀና በተቀናጀ የትምህርት ልማት ሰራዊት አግባብ አጠናክረን መሄድ ይገባናል ያሉት አቶ አብዱልማሊክ  ከዚህም በተጨማሪ በጎልማሶችና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ዙሪያ ያሉ የተደራሽነትና የፍትሀዊነት ክፍተቶችን በመለየት፤ ከኤሊኖ ክስተት ጋር ተያይዞ በትምህርት ዘርፉ የተከሰቱ ችግሮችን ለመሙላት የሚያስችል አቅጣጫ ማስቀመጥ ከዚህ መድረክ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።  ከድህነትና መሀይምነት አዙሪት ወጥተን ፈጣንና ዘላቂ ፤ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለንተናዊ እድገት በማረጋገጥ የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት በምናደርገው የለውጥ የሽግግር ሂደት፤ጥረትና ስኬት ትምህርት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው ያሉት ደግሞ የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አፈንዲ አብዱልዋሲ ናቸው።

13 - GE Meeting Harar Pic-1

እያንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት እንደ አቅሙ ሊሳተፍ የሚችለው የዳበረ እውቀትና ክህሎት ሲኖረውና በተግባር ሲያውለው ብቻ በመሆኑ የምናቀርበው ትምህርት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ አፈንዲ ክልሉ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ዜሮ ክፍሎችን በመክፈት የቅድመ መደበኛ ተሳትፎን 81.8 በመቶ እንዲሁም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን 104.1 በመቶ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል። የግምገማ መድረኩ በጎልማሶችና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ያሉ የፍትሃዊነት ክፍተቶችን፣ የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የመምህራን አቅም ግንባታ፣ የትምህርት ቤት ማሻሻያ መርሃ ግብርና የመጻህፍት ጥምርታ ያሉበትን ሁኔታ  በጥልቀት በመፈተሽ የተወያየ ሲሆን የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣዮቹ  ወራት የተጠናከረ ስራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ እንደተናገሩት የአጠቃላይ ትምህርት መርሃ ግብር  በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው  የቀጣዮቹ ወራት የትኩረት አቅጣጫ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ እያንዳንዱ ክልል ባሉት የትምህርት መዋቅሮች በአምስተኛው የትምህር ዘርፍ የልማት መርሃ ግብር/ESDP V/ እንዲሁም በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦች ላይ መግባባት በመፍጠር ለዕቅዶቹ መሳካት ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

በቅድመ መደበኛ ትምህርት ያለፉ ተማሪዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው  የቅድመ መደበኛ ትምህርት መምህራን ስልጠና በጥናትና በዕቅድ ሊመራ ይገባል ብለዋል፡፡  የትምህርት ልማት ሰራዊት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ የተጠናከረ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ዶ/ር ጥላዬ ሁሉም የልማት አቅሞቻችን ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ መምህራን ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለብን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የመምህራን የደረጃ ዕድገት ጉዳይ በመንግስት እየታየ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡  ለሶስት ቀናት በተካሄደው የግምገማ መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል በስተቀር የሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የአጠቃላይ ትምህርት የስድስት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡


News

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡