የትምህርት ዘርፍ ልማት የአምስት አመት እቅድ በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ይተገበራል

የትምህርት ዘርፍ ልማት የአምስት አመት እቅድ በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ይተገበራል

የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ዳር ለማድረስ የአምስት ዓመቱን የትምህርት ዘርፍ ልማት እቅድ በተናበበና በተቀናጀ መልኩ መተግበር ተገቢ እንደሆነ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ አስታወቁ፡፡

በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ ለአራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሀገራዊ የህዝብ የንቅናቄ መድረክ መገባደጃ ላይ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ የአምስት ዓመቱን የትምህርት ዘርፍ ልማት እቅድ ለንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊዎች ባቀረቡበት ወቅት ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ በብቃትና በጥራት በማፍራት የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ እቅዱን ከክልል እስከ ት/ቤት ድረስ የጋራ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡Images

እቅዱ የትምህርት ሽፋንን፣ ተደራሽነትን፣ ተገቢነትንና ጥራትን በማሻሻል የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነት ለመቅረፍ ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ሚንስትር ዴኤታው በንቅናቄ መድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻና አጋር አካላት እቅዱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የንቅናቄ መድረኩ አንዳንድ ተሳታፊዎች በበኩላቸው እቅዱ ሀገሪቱ ለምታደርገው የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያስፈልግ የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት ለማፍራት አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

በተለይም ጎልማሶችን ከማይምነት ለማላቀቅ ቢያንስ በመጻፍ፣ በማንበብና በማስላት እንዲሁም የህይወት ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ የ2012 የሀገሪቱን የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውጤታማ ያደርገዋልም ብለዋል ተሳታፎዎቹ፡፡

እቅዱ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የተጠያቂነት ስርዓት ሊኖር እንደሚገባና የሚመለከታቸው አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የገለጹት ተሳታፊዎቹ በዋናነት መንግስት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት የማስፈን፣ የመምህራንን ጥያቄ እየተከታታለ ምላሽ በመስጠት ሙያው የተከበረ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም የትምህርት ቤቶችን ግብአት ማሟላት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡም ት/ቤቶችን በባለቤትነት የመምራት፣ የማስተዳደርና ደረጃቸውን በማሻሻል፣ ራሱንና ልጆቹን ት/ቤት እንዲውሉና ለት/ቤት ግብዓት መሟላት ትኩረት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ጠቅሰው መምህራንም ለተመረቁበት ሙያ እና ለሚያስተምሩት ትምህርት ብቁና ታማኝ በመሆን ለተማሪዎች ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ማስጨበጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡Images

በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ ለአራት ተከታታይ ቀናት ለውይይት በቀረቡት አምስት ሰነዶች የአጠቃላ ትምህርት ጉዳዮችን በያዘው የ2009 ዓ.ም የህዝብ የንቅናቄ ማቀጣጠያ ሰነድ፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት እቅድ፣ በመምህራንና የትምህርት የአመራር ሙያ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያና ማስፈጸሚያ ሰነዶች፣ በስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት አሰጣጥና የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚናና ሊኖረው በሚገባ ቁመና በሚል ሰነዶችና በት/ቤቶች ኢንስፔክሽና ደረጃ ፍረጃ መመሪያዎች ላይ ከተወያዩ በኋላ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት የላቀ ለማድረግ በሁሉም ክልሎች ተመጣጣኝ የሆነ የተደራጀ የትምህርት ልማት ሰራዊት ማጠናከርና የማስፈጸም አቅሙን የመገንባት፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በፍትሀዊነት ለማስፋፋትና እድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት እንዲገቡና እንዲዘልቁ፣ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጆችን በመተግበር የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ላይ ለውጥ ለማምጣት፣ ተጠያቂነትን በማስፈን ለኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉትን አሰራሮች በመለየት በቁርጠኝነት ለመታገል እንዲሁም ሌሎች ለትምህርት ፍትሀዊነትን፣ ተገቢነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ሀሳቦችን ጨምሮ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የንቅናቄ መድረኩ ተጠናቋል፡፡


News

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡