በሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤታማ ለማድረግ የሴት ተማሪዎች እገዛ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤታማ ለማድረግ የሴት ተማሪዎች እገዛ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሚደረግላቸው እገዛ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ነጥብ እያስመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ-ጾታና ባለዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀይማኖት በተቋም ደረጃ ገና ወደ ግቢ ለሚመጡት ተማሪዎች ከእንኳን ዳህና መጣችሁ አቀባበል ጀምሮ እገዛ ይደረግላቸዋል፣ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ለሌሎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ይደረጋል፣ የግቢ ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደት እና ፋሲሊቲዎች አጠቃቀም ሁኔታ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ይሰራል፣ የግቢ ቆይታ የህይወት ክህሎት እና ተመሳሳይ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ለብቻ ይሰጣቸዋል፣ ከትምህርት ክፍል ምርጫ ጀምሮ በተለይ በሳይንሱ ትምህርት በኩል ብቁ እንዲሆኑ ከመምህራንና ከኮሌጆች ጋር በመመካከር ይሰራል ብለዋል፡፡ በዚሁም የነበረባቸውን ጫና በማስወገድ የይቻላል መንፈስ ይዘው ከወንዶች እኩል እንዲሳተፉ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

በዚሁ ድምር ትብብር ውጤት ሴት ተማሪዎቻችን የላቀ ውጤት በማስመዝገብ በተለያዩ አካላት ጭምር እንዲሸለሙ አድርጓቸዋል፣ እየተሸለሙም ይገኛሉ ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጂነርንግ ትምህርት ክፍል መ/ርት ብርሃኔ ጌታቸው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመምህራንና የቤተሰብ ድጋፍ ወሳኝነት እንዳለው ይገልጻሉ፡፡የራሳቸውን ልምድ በማካፈል ልጆች ወይም ተማሪዎችን መርዳት ዝንባሌ እንዲኖራቸው፣ የሂሳብ ትምህርት ፊላጎት እንዲያድርባቸው፣ ከተለመደው አንብቦ ወይም ሸምድዶ የተማሩትን አስታውሶ ለፈተና ከመቅረብ በላይ የወደፊት ሙያቸውንም እንዲያስተካክሉ ጭምር ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡በሙያቸውም የበቁ በራሳቸው የሚተማመኑ ሙያተኞች ሆነው እንደሚቀረጹ ጭምር ይረዳቸዋል ይላሉ፡፡

የተለመደው አሁንም እየተሰጠ ባለው የሀገራችን የትምህርት አሰጣጥ ስነ-ዘዴ ተማሪዎች የተማሩትን በሽምደዳ በማስታወስ ከመፈተን ውጭ ወደ ተግባር የመቀየር ዕድሉ በጣም አናሳ ነው ይላሉ መምህርቷ፡፡ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትኩረት ከተሰጠው የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሴት ተማሪዎች ላይ የሚያሳርፈው የስነ-ልቦና ጫና እንደሚቀንስ ይናገራሉ፡፡

ያነጋገርናቸው የዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎችም የሃላፊዋንና የመምህረቷን ሀሳብ እንደሚጋሩ ገልጸዋል፡፡


News

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡